የፈረንጆችን የእረፍት ጊዜ ምክንያት በማድረግ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያነቃቃው አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የቱሪዝም ሚንስቴር ሚንስትር አስታወቁ፡፡
ሚንስትሯ ይህን የገለጹት ዛሬ በ ስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሀገራችንን ገጽታ ለሚያበላሹ ሀገራትና ታላላቅ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ድምጽ በመሆን ሀገራቸውን በመታደግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
አያይዘውም ወደ ሀገራቸው በመምጣት የሀገራቸውን ገጽታ እና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ኢትዮጵያ የሚመጡ መሆኑን ሚንስትሯ ጠቁመው ይህ ዂነትም ለቱሪዝም መልካም ዕድል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሚመጡ ዲያስፖራዎች ጦርነት ተደርጎባቸው ነጻ የወጡትን ክልሎች ሰላም መሆናቸውን መጥተው ካዩ በኋላ ለጓደኞቻቸውና ለወዳጆቻቸው በማስገንዘብ የሀገር ገጽታ ግንባታ ሥራና የቱሪዝም ዘርፍን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰሩ ይታመናል፡፡ ዲያስፖራዎቹን ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት መጀመሩን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ጠቁመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሆቴሎች እና አስጎብኝ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እስከ 30 በመቶ ቅናሽ ያለበት አገልግሎትና መስተንግዶ ለመስጠት መስማማታቸውን ሚንስትሯ ገልጸዋል ፡፡
ለመርሐ ግብሩ ስኬት ብሔራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የፓኬጅ ቀረጻ ሥራ መከናወኑ ታውቋል፡፡ የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ እና አፕሊኬሽኖችን በመጠቀም እና በተለያዩ መደበኛ እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡በተጨማሪም ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሌሎች ሀገር አቀፍ ዂነቶች እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡