በታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎች በሚኖራቸው ቆይታ የሚሳተፉባቸውን መርሃ ግብሮች ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የብሄራዊ ኮሚቴው የኦፕሬሽናል ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን አንስተው፣ ዳያስፖራው ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ በሚችለው ነገር ሁሉ አኩሪ ተግባር ሲያከናውን እንደነበር አስታውሰዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም የአሁን ጥሪ ዳያስፖራው ሀገሩንና ወገኑን በዘላቂነት እንዲያግዝ መሰረት የሚጣልበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጥሪውንና ዳያስፖራው የመጣበትን አላማ ማሳካት የሚያስችሉ መርሃግብሮችም መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።የብሔራዊ ኮሚቴው ሴክሬታሪያትና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስም ከታለቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ኮሚቴው የጸደቀውን የሁነት መርሃ ግብር አቅርበዋል። በዚህም መሰረት ታህሳስ 20፣2014 ዓ/ም በወዳጅነት ፓርክ ይፋዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም እንደሚኖር ገልጸዋል። የ
መክፈቻ ስነ ስርዓቱን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በክልሎች የሚከናወኑ ሁነቶችን በዝርዝር አቅርበዋል (የሁነቶቹን ዝርዝር ከዚህ ዜና በኋላ ራሱን አስችለን የምናቀርብ መሆናችንን እንገልጻለን)።የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው ዳያስፖራው በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ በአግልግሎት አሰጣጥ ላይ ያልተፈለገ ችግር እንዳይገጥመው በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
ይህንን አስምልክቶም ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተገቢ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።የብሄራዊ ኮሚቴው አባል የሆነውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በመወከል የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ም/ከንቲባ ክቡር አቶ ዣንጥራር ዓባይም ዳያስፖራው በቆይታው ያለ ምንም እንግልት የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች እንዲያገኝ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። ከተማው ውስጥ የሚደረጉ ኩነቶችም ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ ለማድረግ የተቀናጀ የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑንም ጠቅሰዋል።